ስለ
ሚኒስቴሩ
በኢትዮጵያ ከትላልቅ እስከ መካከለኛ እርሻዎችን ለማልማት መስኖ ጥቅም ላይ ሲውል ቆይቷል። ይሁን እንጂ ለአገሪቱ የግብርና ዘርፍ እና አጠቃላይ የኢኮኖሚያዊ ልማት ላይ ከሚፈጥረው ዕድል አንፃር ሲታይ አሁንም የሚጠበቀውን ያህል ጥቅም ላይ አልዋለም። በተጨማሪም ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2023 መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለመሰለፍ ባስቀመጠችው ግብ መሰረት የተፈጥሮ ሀብትና የመስኖ ቴክኖሎጂን በአግባቡ መጠቀም ይህንን ራዕይ እውን ለማድረግ ያስችላታል።
መመሪያ
ከግብርና እና ውሃና ኤነርጂ ሚኒስቴር ጋር በመተባባር የአርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች ውሃን ማዕከል ያደረጉ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች እንዲስፋፉ ያደርጋል፣ የመስኖ ልማቶች እንዲስፋፉ ያደርጋል፤
በተቀናጀ የተፋሰስ ልማት በውሃና ኤነርጂ ሚኒስቴር ጥናት የተለዩ የሀገሪቱን የከርሰ ምድር እና የገጸ-ምድር የውሃ ሀብት ለመስኖ ልማት የሚውልበትን ሁኔታ ያመቻቻል፤
የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶችን ምርታማነት በሚያሳድጉ ወቅታዊ ቴክኖሎጂዎች እንዲደገፉና ውሃ ቆጣቢ አሠራር እንዲከተሉ ያበረታታል፤
የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ፋይናንስ እንዲያገኙ በተለያዩ ዘዴዎች ያስተዋውቃል፤ ሕግን መሠረት በማድረግ ባለሀብቶች ማትጊያ እንዲያገኙ ሁኔታዎችን ያመቻቻል፤
አርብቶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮች የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራትን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ያስተባብራል፤
በተፋሰሶች ውስጥ የሚደረጉ የመስኖ ማስፋፋት ሥራዎችን ለመደገፍ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት ይሠራል፤