የኢትዮጵያ ቆላማና አርብቶአደር አካባቢዎች ለግብርና ምርትና ልማት አስተዋፅኦ ለማድረግ እንዲሁም ለምግብ እና ለኢንዱስትሪ ሰብል ምርት የተቀመጡ ሃገራዊ ግቦችን ከማሳካት አንፃር ከፍተኛ አቅም አላቸው። የኢትዮጵያ መንግስት ለዚህ ሃገራዊ አላማ የቆላማና አርብቶአደር አካባቢዎች የልማት ጥረቶችን ለማሳካት እና የኑሮ ተግዳሮችን በተጨባጭ ለመቅረፍ የተሻለ የምግብ እና የአመጋገብ ዋስትናን፣ የስራ ዕድል ፈጠራን እና ገቢን የማሳደግ ስራዎችን በብቃት ለመወጣት ቁርጠኝነቱን በድጋሚ ያረጋግጣል።
የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር በኢትዮጵያ ቆላማ አካባቢዎች ድርቅን የሚቋቋም ኑሮን የመገንባትና የማሳደግ ስትራቴጂ ነድፏል። በዚህ ስትራቴጂ መሰረት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የቆላማና አርብቶአደር አካባቢዎች ልማት ፕሮጀክት ክንፍ በዋናነት የቆላማና አርብቶአደር አካባቢዎች የግብርና፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎችን በዘላቂነት ለመለወጥ የሚረዳ ዘርፈ ብዙ መርሃ ግብርን በመተግበር ድህነትን ለመቅረፍ እና የአየር ንብረት መዛባትን ለመቀነስ የበኩሉን ድርሻ ይይዛል።
ሚኒስቴሩ ዋና የትኩረት አቅጣጫዎችን የማውጣት ኃላፊነት አለበት፤ ይህም ከክልል መንግስታት እና ከዋና ዋና ባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት በመጣመር አቅማቸውን የማሳደግ እና ለቆላማና አርብቶአደር አካባቢዎች ልማት ስኬታማ አፈፃፀም አስፈላጊ የቴክኒክ ድጋፍ በማድረግ የሚከናወን ነው።
የግሉ ሴክተር ተሳትፎ ወሳኝና ለቆላማና አርብቶአደር አካባቢዎች ልማት ለሚከናወኑ ጥረቶች አንኳር ሚና ይጫወታል። በዚህ ረገድ ሚኒስቴሩ በቅንጅት ለመስራት ሁኔታዎችን በማመቻቸት ግንባር ቀደምነትን ይይዛል። ስለሆነም ሁሉም የግሉ ሴክተር እና የልማት አጋሮች በዚህ ጉዞ ከሚኒስቴሩ ጋር እንዲተባበሩ እና የቆላማ አካባቢዎች ዘላቂነት ያለው አኗኗር እንዲገነቡ የበኩላቸውን ሃላፊነት እንዲወጡ በአክብሮት እጋብዛለሁ።