ሚኒስቴሩ ከዓለማቀፉ ሃይፈር ፕሮጀክት ኢንተርናሽናል ጋር በጥምረት ለመስራት ስምምነት ተፈራረመ
News
በዛሬው ዕለት በመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር በተከናወነው ስነ-ስርዓት ላይ ስምምነቱን የተፈራራሙት ክብርት ሚኒስትር ኢ/ር አይሻ መሃመድና የሃይፈር ፕሮጀክት ኢንተርናሽናል ፕሬዚዳንትና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሶሪታ ሳንዶሻ ናቸው፡፡
በዚሁ ስነ-ስርዓት ላይ ክብርት ሚኒስትሯ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ የአየር ንብረትን መሰረት ያደረጉ ዘላቂ የልማት ተግባራትን ለመተግበር በምታደርገው ጥረት ከሃይፈር ፕሮጀክት ኢንተርናሽናል ጋር የተደረገው የትብብር ስምምነት ትልቅ አቅምን የሚፈጥር ነው፡፡
ስምምነቱ በተለይም የቆላማና አርብቶ አደር የልማት ስትራቴጂ በመንደፍ፣ በአነስተኛ አርሶአደሮች ደረጃ የእንስሳትና ተዋፅኦ ሃብቶችን ገበያ መር ከማድረግና የገበያ ሰንሰለቶችም ውጤታማ በሆነ መልኩ ከመዘርጋት አኳያ ትልቅ ሚና እንደሚኖረውና በግሉ ሴክተር የሚመራ አዋጭ የመስኖ ፕሮግራሞችን ለመተግበር ትልቅ ሚና ይኖረዋል፡፡
የሃይፈር ፕሮጀክት ኢንተርናሽናል ፕሬዚዳንትና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሶሪታ ሳንዶሻ በበኩላቸው ከሚኒስቴሩ ጋር በትብብር በመስራታቸው መደሰታቸውን ገልፀው ሃይፈር ፕሮጀክት ኢንተርናሽናል ለአርሶ አደሮች ተደራሽና ዘላቂ የገበያ ትስስሮችን ለመዘርጋት ባለው ዓላማ መሰረት ሚኒስቴሩ በሚያከናውናቸው ተግባራት በዘላቂነት አብሮ ለመስራት ቁርጠኛ መሆናችንን እናረጋግጣለን ብለዋል፡፡
ሃይፈር ፕሮጀክት ኢንተርናሽናል ለትርፍ ያልተቋቋመና ከአነስተኛ አርሶ አደሮች ጋር በተያያዘ ረሃብንና ድህነትን በዘላቂነት ለማስወገድ የሚሰራ ተቋም ነው፡፡
የጨልጨል መስኖ ልማት ፕሮጀክት በ5.15 ቢሊዮን ብር ግንባታው እየተከናወነ ነው ፡፡
News
በመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ባለቤትነት የጨልጨል መስኖ ልማት ፕሮጀክት በ5.15 ቢሊዮን ብር ግንባታው በኦሮሚያ ክልል በምስራቅ ባሌ ዞን በራይቱና ጊኒር ወረዳዎች እየተከናወነ ይገኛል፡፡ ይህ ፕሮጀክት ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ 4146 ሄክታር በማልማት ከ9000 በላይ አርብቶአደሮችና ከፊል-አርብቶአደሮችን ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡
የጨልጨል ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት የሚገነባው በራይቱና ጊኒር ወረዳዎች አዋሳኝ ቦታ የዌብ ወንዝ ገባር በሆነው በጨልጨል ወንዝ ላይ ሲሆን የመስኖ ልማት አውታሮች ደግሞ በራይቱ ወረዳ ውስጥ ነው ፡፡
የጨልጨል ግድብ ከፍታው 46.5 ሜትር፣ ርዝመቱ 681 ሜትር ሲሆን ግደቡ 50 ሚሊዮን ሜትር ኩብ ውሃ በመያዝ 341.8 ሄክታር ቦታ በውሃ ይሸፈናል ፡፡ እንደዚሁም እስከ 1.5 ኪሎ ሜትር ወደ ኋላ ውሃው ይተኛል፡፡
ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ በራይቱ ወረዳ በዓመት ውስጥ የተለያዩ ሰብሎችን በቆሎ ፣ ስንዴ፣ ማሽላ ፣ፓፓያ ፣ሙዝ ፣ሽንኩርትና ቲማቲም የመሳሰሉትን ከ 2—3 ጊዜ ማምረት ያስችላል ፡፡
የግድብና የመስኖ ልማቱ ግንባታ በዋናነት የሚያካትተው 47.5 ኪሎ ሜትር ዋና ቦይ ሲሆን 3.5 ኪሎ ሜትር ከተገነባ በኃላ በግራ 21.5 ኪሎ ሜትር እና 22.6 ኪሎ ሜትር በቀኝ የሚገነባ ይሆናል ፡፡ በተጨማም 35.2 ኪሎ ሜትር ሁለተኛ ቦይና 168 ኪሎ ሜትር 3ኛ ቦይ ይገነባል ፡፡
ፕሮጀክቱ በሁለት ሎት ተከፍሎ የሚሰራ ሲሆን ሎት አንድ የግድብ ግንባታና ተያያዥ ስራዎችን ግንባታን ሲያከናውን የነበረው የመጀመሪያው ስራ ተቋራጭ ድርጅት ስራውን ከአቋረጠ በኃለ አለማየው ከተማ ጠቅላላ ስራ ተቋራጭ ድርጅት ስራውን ለመስራት የኮንትራት ውል ገብተዋል፡፡ ይህ ስራ ተቋራጭ ድርጅት ስራውን ለመጀመር የማሽነሪና የሰው ሃይል ሞቢላይዜሽን ጀምረዋል፡፡ እንዲሁም ሎት ሁለትን የመስኖ መሬት ዝግጅት፣ ዋና ካናልና ተያያዥ ስራዎችን ግንባታውንም እያከናወነ ያለው የኦሮሚያ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ነው ፡፡ ይህ ድርጅት ከአሁን በፊት ኮንትራቱ ለሁለት ጊዜ የተራዘመለት ሲሆን በቶሎ አስፈላጊውን ማሽነሪ አስገብቶ ማይሰራ ከሆነ ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ ማጠናቀቁ አዳጋች ሊሆን ይችላል፡፡
የፕሮጀክቱ ግንባታ በ2015 በጀት ዓመት መጋቢት ወር መጨረሻ ድረስ የሎት አንድ 13.68 % እንዲሁም ሎት ሁለት 74.75% ደርሰዋል፡፡
በፕሮጀክቱ ወንድ 430 ሴት 79 በጠቅላላው 509 ዜጎች ጊዝያዊና ቋሚ የሥራ እድል አግኝተዋል፡፡
የፕሮጀክቱ ተግዳሮቶች የንዑስ ተቋራጭ ድክመት ፣የጉልበት ሰራተኛ እጥረት እና የማሽን ዕጥረት ሲሆኑ ችግሩን መፍታት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደርገዋል ፡፡
ፕሮጀክቱ በታህሳስ 2012 የተጀመረ ሲሆን በ2018 በጀት ዓመት መጨረሻ ለማጠናቀቅ ታቅዶ እየተሰራ ነው፡፡
የወይቦ መስኖ ልማት ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ 3,429 ሄክታር መሬት የማልማት አቅም አለው፡፡
News
በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በወላይታ ዞን በወይቦ ወንዝ ላይ በ2.44 ቢሊዮን ብር የሚገነባው የወይቦ መስኖ ልማት ፕሮጀክት ሕዳር 2014 ዓ/ም የተጀመረ ሲሆን ሲጠናቀቅ 3,429 ሄክታር መሬት የማልማት አቅም አለው፡፡
ፕሮጀክቱ የሚገኝበት ቦታ ወላይታ ዞን አስተዳደር ሲሆን ግድቡ የሚገነባው በቦሎሶ ሶሬ ወረዳ እንዲሁም የመስኖ መሰረተ ልማቱ በቦሎሶ ሶሬ ወረዳና በቦሎሶ ቦምቤ ወረዳዎች ውስጥ ነው፡፡
ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ በቦሎሶ ሶሬ ወረዳ 4 ቀበሌዎችና በቦሎሶ ቦምቤ ወረዳ 7 ቀበሌዎች ውስጥ የሚገኙ ከ12,000 በላይ አርሶ አደሮችን በቀጥታና በተዘዋዋሪ ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡
የወይቦ መስኖ ልማት ፕሮጀክት የግድቡ ርዝመት 660 ሜትርና የግድቡ ከፍታ 32.7 ሜትር ሲሆን 630 ሄክታር ላይ ውሃው ወደ ኃላ የሚተኛ ሲሆን ይህም ለቱሪስት መስህብነትና ለዓሳ ምርት ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ 60 ሚሊዮን ሜትር ኩብ ውሃ የመያዝ አቅም አለው፡፡
ፕሮጀክቱ እስከ መጋቢት ወር 2015 ዓ/ም መጨረሻ ድረስ አጠቃላይ አፈፃፀሙ 11.3 % ተከናውነዋል፡፡
የፕሮጀክቱ ተግዳሮቶች የካሳ ግምት መጋነንና ክፊያ መዘግየት፣ የስራ ተቋራጮችና አማካሪ ድርጅት አቅም ውስንነት ሲሆኑ ችግሩ እንዲፈታ ከሚመለከታቸው ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶች ተካሄደዋል፡፡
ፕሮጀክቱ በሁለት ሎቶች ተከፍሎ የሚገነባ ሲሆን ሎት-1 (የግድብና ተያያዥ ሥራዎች ግንባታ) በደቡብ ውሃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት እንዲሁም ሎት-2 (የመስኖ መሬት ዝግጅት ግንባታ) የሚገነባው ክሮስ ላንድ ኮንስትራክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ከኦሮሚያ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ጋር በጆይንት ቬንቸር በመቀናጀት ነው፡፡
የፕሮጀክቱ ተቆጣጣሪ መኃንዲስ የደቡብ ዲዛይንና ቁጥጥር ኢንተርፕራይዝ ነው፡፡